Welcome to
Announcement በህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መብትና ክብራችን ተጠብቆ ለመሰማራት ስልጠና እየተከታተልን ነው - ሰልጣኝ ወጣቶች

በህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መብትና ክብራችን ተጠብቆ ለመሰማራት ስልጠና እየተከታተልን ነው - ሰልጣኝ ወጣቶች

09th August, 2025

በህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መብትና ክብራችን ተጠብቆ ለመሰማራት ስልጠና እየተከታተልን ነው - ሰልጣኝ ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2017(ኢዜአ)፦ በህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም መብትና ክብራችን ተጠብቆ የሥራ ስምሪት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በውጭ ሀገር ሥራ ለመሰማራት በአዲስ አበባ ስልጠና የሚከታተሉ ወጣቶች ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ በህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎች መብትና ክብራቸው እንዲጠበቅ የማድረግ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ በሀገር ውስጥ ምቹ የሥራ ዕድሎችን ማስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ የመሥራት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች መብታቸው ተከብሮ እንዲሄዱ መንግሥት አሰራሮችን ሲዘረጋ ቆይቷል።
ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም ሰርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሂደቱን የሚመራ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ የወጣ ሲሆን፥ ዘመኑን የዋጁ ድንጋጌዎች እንዲኖሩት በማሰብ በያዝነው ዓመት ተሻሽሎ ጸድቋል።
መንግሥት ከዚህም ባለፈ ህጋዊ የሥራ ስምሪትን ለማጠናከር ኢትዮጵያውያን ከሚሰማሩባቸው ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የአሰሪና ሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በመፈራረም እየሰራ ይገኛል።
በውጭ ሀገር በህጋዊ የሥራ ስምሪት የሚሰማሩ ዜጎች ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ሙያና ክህሎት እንዲኖራቸው የሥልጠና ማዕከላት ተከፍተው ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።
ኢዜአ በስልጠና ማዕከላቱ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ሰልጣኞች እንደሚሉት፥ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረግ የሥራ ስምሪት ጉዳት እንደሚያስከትል በመገንዘብ በህጋዊ መንገድ መብታቸው ተጠብቆ ለመሰማራት ተዘጋጅተዋል።
ከሰልጣኞች መካከል ሄለን ዳንኤል እና ማሜ ግዛው ህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አሰራሩ በቂ ስልጠና አግኝተን፣ ደህንነታችንና መብታችን ተጠብቆ እንድንሄድ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሄዋን ደበበ እና ሳምራዊት ተፈራ ህገወጥ ስደት አደገኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ መሄድ የሚፈልጉ ዜጎች በህጋዊ መንገድ በመሄድ የተመቻቸውን እድል መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ለሥራው በቂ የሙያና ክህሎት ስልጠና እያገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው፥ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሠራተኛ ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር ህጋዊ ስምምነት በመፈፀም ክህሎት ያላቸዉ ዜጎች መብታቸው፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ የሥራ ዕድል የሚያገኙበት አሠራር መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም ሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ማጠናከር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
መንግሥት ይህን አሠራር በህግ እና በአዋጅ እንዲሁም በቴክኖሎጂ በመደገፍ በስፋት እየሠራበት እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ዜጎች የሙያና ክህሎት ስልጠና ወስደው የሁለትዮሽ ስምምነት ወደተደረሰባቸው ስድስት ሀገራት የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሀገራቱም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ጆርዳን እና ሊባኖስ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ወደ ውጭ ሀገር መሰማራታቸውን ነው የተናገሩት።
የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመፈፀም ሂደቱ ቀላል እንደሆነ በመግለጽ፥ ዜጎች አስፈላጊ የሆኑ የስልጠና፣ የሜዲካል፣ የቪዛ እና ትኬት ጉዳዮችን ጨርሰው እንዲሄዱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለዚህም ህጋዊ ፈቃድ ካላቸው ኤጀንሲዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዜጎች ደህንነትና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲሰማሩ በመንግስት የተዘረጋውን ህጋዊ የስራ ስምሪት እድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸውም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስገነዘቡት።
.

Copyright © All rights reserved.