ለሁለት ቀናት የሚቆይና ወጣቶችን ከሥራ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ የሥራ አውደ ርዕይ ተከፈተ።
🌼መስከረም 26/2019 ዓ.ም🌼
የአዲስ አበባ ሠራተኛና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ እና ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ያዘጋጁት 110 ቀጣሪዎች የተካፈሉበት የሥራ አውደ ርዕይ በአድዋ ድል መታሰቢያ ተከፍቷል፡፡
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሠራተኛ እና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ሥራ እድል የመፍጠሩ ተግባር የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የግል ዘርፉም ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊው ከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች በቴክኒክ ሙያ ኮሌጆችና የልህቀት ማዕከል ክብር ያለው ሥራ እንዲሁም ብቁ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ አውደ ርዕዩ ለሁለት ቀናት የሚቆይና ወጣቶችን ከሥራ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በአውደ ርዕዩ 110 ድርጅቶች የተሳተፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ አዲሱ እሳቤ ሰልጣኖችን ማስመረቅ ብቻ አለመሆኑን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ የተለያዩ የሥራ አማራጮችን በማመቻቸት ተመራቂዎችን ከሥራ ጋር ማስተሳሰር ሌላኛው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአውደ ርዕዩ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በ2018 የስልጠና ዘመን ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞች ወደ ተዘጋጁላቸው የቀጣሪ ድርጅቶች በመቅረብ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ያላቸውን ክህሎትና መረጃ በማካፈል ለሥራ ዕድል እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

.