16ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በደመቀ ስፖርታዊ ውድድር ተከፈተ።
🇪🇹አዲስ አበባ | መጋቢት 29/2018 ዓ.ም🇪🇹
"የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው 16ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት፣ ስፖርታዊ ውድድር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይህ ስፖርታዊ ውድድር ማስጀመሪያ፣ በመክፈቻው ዕለት ከ5000 በላይ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ታላቅ ስፖርታዊ ውድድር አስተናግዷል።
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚደክሳ ከበደ፤ ሀገራችን ያስመዘገበችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል ልማታዊ አስተሳሰብ ያለውና በክህሎት የዳበረ አምራች ዜጋ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስልታዊ አካሄዶችን እየተገበረ መሆኑንም አክለዋል።
እንደ አቶ ሚደክሳ ማብራሪያ፤ ይህ ዓመታዊ አውደ-ርዕይ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በአሰልጣኞችና ሰልጣኞች የተሰሩ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች፣ የውጭ ምርትን የሚተኩ የኢንተርፕራይዞች ውጤቶች እንዲሁም የፈጠራ ስራዎች የሚቀርቡበት ታላቅ መድረክ ነው። ከቴክኖሎጂ፣ ከክህሎትና ከፋሽን ዲዛይን ውድድሮች በተጨማሪ በዛሬው ዕለት የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድር በኮሌጆች መካከል ያለውን ትውውቅ ለማጠናከርና "ብቁና ንቁ የፐብሊክ ሰርቫንት" ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስግደው ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ "የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው" ብለዋል። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የዚህ ጉዞ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የቴክኖሎጂ ልህቀት ያለ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ሙሉ ሊሆን ስለማይችል ስፖርት ለዚህ ዘርፈ ብዙ ስኬት አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህ ስፖርታዊ ውድድር በ15 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መካከል የሚካሄድ ሲሆን፣ ለሚቀጥሉት 15 ቀናት በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ በገመድ ጉተታና በቮሊ ቦል ዘርፎች ውድድሮች ይካሄዳሉ። ይህም ተቋማዊ ትብብር ለወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሁለቱም ቢሮዎች ማኔጅመንት አባላት፣ የሁሉም ኮሌጆች አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቦች ተወዳዳሪዎች በነቂስ ተገኝተዋል።<<ከፍታን ማፅናት፤ ነገን ማላቅ>>


.