130ኛው የአድዋ ድል በዓል በስራና ክህሎት ቢሮ ስር በሚገኙ ክላስተር ኮሌጆች በፓናል ውይይት ተከበረ፡፡
የካቲት 9/2018 ዓ.ም
የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና እና የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ኩራት የሆነው 130ኛው የአድዋ ድል በዓል ‹‹የአድዋ አደራ፡ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ማንሰራራት›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ስር በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።
በቢሮው ስር በሚገኙ በተግባረዕድ፣ በዊንጌት እና በንፋስ ስልክ ክላስተር በተዘጋጁ የፓናል ውይይቶች ላይ የተጠሪ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተሳታፊ ሆነዋል። በመድረኮቹ ላይ ከ4500 በላይ የኮሌጅ ዲኖች፣ አሰልጣኞች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተገኝተው በድሉ ታሪካዊ ፋይዳና ወቅታዊ አደራ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ክላስተር በተካሄደው መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ለሆነው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት የህዝቦችን አንድነት እና የሀገርን ግንባታ ለማጠናከር፣ ይህ ትውልድ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በጀግንነት እና በአርአያነት ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።
አቶ ሚዴቅሳ አክለውም "የትናንቱን ጀግንነትና አርበኝነት ማውደሳችን ትርጉም የሚኖረው ዛሬ ላይ ያለብንን ድርሻ ተወጥተን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ህያው ስራ መስራት ስንችል ነው" በማለት የድሉን አደራ አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ላይ የቀረቡት ሰነዶች የአድዋ ድል በመሪዎችና በህዝብ አንድነት የተገኘ መሆኑን ዳስሰው ይህም የታሪክ አደራ በስራ ቦታና በቴክኖሎጂ ሽግግር ሊደገም እንደሚገባው አሳስበዋል። በተለይም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች በምርታማነት ረገድ የሚያሳዩት ጥረት የሀገርን ሉዓላዊነት በኢኮኖሚ ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በመድረኩ ተገልጿል።
ተሳታፊዎቹም የአድዋን መንፈስ ወደ ስራና ውጤታማነት በመቀየር፣ የተጣለባቸውን የሀገር ብልጽግና አደራ ለመወጣት ቃል በመግባት መርሃ ግብሩን አጠናቀዋል።

.