Welcome to
Home በአዲስ አበባ በክላስተር ደረጃ የሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ክህሎት ውድድር በጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተካሄደ፡፡

በአዲስ አበባ በክላስተር ደረጃ የሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ክህሎት ውድድር በጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተካሄደ፡፡

20th February, 2026

በአዲስ አበባ በክላስተር ደረጃ የሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ክህሎት ውድድር በጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተካሄደ፡፡

የካቲት 12/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አስተባባሪነት በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በ6 ክላስተር በ120 ተወዳዳሪዎች መካከል በ20 የውድድር መስኮች የሚካሄደው የክህሎት ውድድር በዛሬው ዕለት ከክላስተሮቹ መካከል አንዱ በሆነው በጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተካሂዷል። 

ውድድሩን በይፋ ያስጀመሩት በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚደክሳ ከበደ እና በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የውጤት ተኮር ሥልጠና እና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ክብርት ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ ናቸው።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ሚደክሳ ከበደ በዘመናዊው ዓለም ያለ ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ሆኖ ዕድገትን ማሰብ የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በቴክኖሎጂ ከቀደሙ አገራት ጋር መወዳደር እንችል ዘንድ በመፍጠር፣ መፍጠንና መዝለል እሳቤ ለሀገር የሚጠቅሙ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት  ማላመድና አዳዲስ ፈጠራዎችን በማከል ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኃላፊው አክለውም የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ በክህሎት የበቁና ቴክኖሎጂን መፍጠርና ማላመድ የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት እንደሆነ ገልጸው  የቴክኒክና ሙያ የክህሎት ውድድር ለከተማዋም ሆነ ለአገር ብሎም ለዓለም የሚተርፍ እምቅ የፈጠራ ውጤት የሚገኝበት መድረክ መሆኑን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት በቴክኒክና ሙያ የሚሰለጥኑ ወጣቶች በክህሎት ውድድሮች ላይ የሚያሳዩት የፈጠራ ብቃት በራሳቸው ሥራ እንዲፈጥሩና በቅጥር ገበያውም እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እንዲሆኑ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህም የሠልጣኞች ጥረት ብቻ ሳይሆን የኮሌጅ አመራሮችና አሰልጣኞች የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ሊሸከም የሚችል ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር እያበረከቱት ያለው የጥራት ሥራ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው 15ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ውድድር ላይ በርካታ ስኬቶችና ሽልማቶች መመዝገባቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ ዘንድሮም በ16ኛው የክህሎት ውድድር ላይ ውጤታማ ለመሆን ውድድሩ በከፍተኛ የሥነ-ምግባር ዲሲፕሊን ሊመራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

.

Copyright © All rights reserved.