ስልጠና በኢንዱስትሪ ባለቤትነት፤ የጄነራል ዊንጌት የ"ዊን-ዊን" WIN-WIN/ አጋርነት ሞዴል
ክፍል 2
መጋቢት1/7/2018 ዓ.ም
በባለፈው ክፍላችን ጄነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አዲሱን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ስትራቴጂ በመከተል ከፕሮጀክት ጥገኝነት ለመውጣት እያደረገ ያለውን ዝግጅት ተመልክተናል። ዛሬ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ፣ ስልጠናን ከኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር በማገናኘት ረገድ የተጀመሩ አዳዲስ አሰራሮችን እንቃኛለን።
ስልጠና በኢንዱስትሪ ባለቤትነት፤ የጄነራል ዊንጌት የ"ዊን-ዊን" WIN-WIN/ አጋርነት ሞዴል የ2017 ዓ.ም የቴ.ሙ.ሥ ስትራቴጂ አንዱ ቁልፍ ግብ የስልጠና ጥራትንና አግባብነትን ማረጋገጥ ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ ስልጠናው በኢንዱስትሪው ፍላጎትና ባለቤትነት (Industry-led) እንዲመራ ማድረጉ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ስትራቴጂው ያስቀምጣል።
የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ መለስ ይግዛው እንደሚሉት፣ ቴክኖሎጂ በየቀኑ በሚለዋወጥበት በዚህ ወቅት መንግስት ብቻውን በየኮሌጁ አዳዲስ ማሽነሪዎችን ገዝቶ ማቅረብ አይችልም። ማቅረብ ካልተቻለ ደግሞ መወዳርም እንደዚያዉ፡፡ መፍትሄው የግል ዘርፉን በስልጠናው ሂደት ውስጥ በቀጥታ ባለቤት ማድረግ ነው።
ኮሌጁ በ"ቤከር ስኩል" (የዳቦ ጋጋሪዎች ማሰልጠኛ) እያሳየ ያለው ተሞክሮ ለዚህ ስኬታማ ማሳያ ነው። በዚህ ማዕከል የግል ኩባንያዎች የሰልጣኞችን ደመወዝ፣ የትራንስፖርትና የግብዓት ወጪ በመሸፈን የራሳቸውን ዘመናዊ ማሽነሪዎች ይዘው እንዲገቡ ተደርጓል። ይህ አሰራር ኮሌጁን ከከፍተኛ ወጪ ሲታደገው፣ ሰልጣኞች ደግሞ በወቅቱ ቴክኖሎጂ እንዲሰለጥኑና ገና ትምህርት ሳይጀምሩ የ"ቅጥር ዋስትና" እንዲኖራቸው አስችሏል። ይህ የቅጥር ዋስትና ተማሪው ተቀጣሪ ብቻ እንዲሆን ሳይሆን፣ በስልጠናው ላይ ያለው ተነሳሽነትና እምነት እንዲጨምር በማድረግ ለስልጠና ጥራት መሻሻል ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አቶ መለስ ገልጸዋል።
የተመልካቾች ተሳትፎ (Comment Section)፦
ክቡራን ተመልካቾቻችን፤ የግል ኩባንያዎች በኮሌጆች ውስጥ ገብተው የማሰልጠኛ ወጪን እንዲሸፍኑና የራሳቸውን ቴክኖሎጂ እንዲያቀርቡ መደረጉ ለስልጠናው ጥራት የሚኖረው አስተዋጽኦ ምንድነው? ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት የቅጥር ዋስትና ማግኘታቸውስ በተነሳሽነታቸው ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? አስተያየታችሁን በኮመንት አጋሩን!

.