<<የስራና ተግባር ትምህርት ስልጠና መርሐ ግብር የትምህርት ስርዓቱን ስብራት በመጠገን በቴክኒካል ክህሎቱ የዳበረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል>>ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ
ታህሳስ 6/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት በከተማዋ የሚገኙ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የስራና ተግባር ትምህርት ስልጠና መርሐ ግብር ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ስልጠናውን ለማስጀመር በሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ ዙሪያ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲኖች እና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የስልጠናው መርሀ ግብር ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ የፈጠራና የሙያ ክህሎትን የሚያሳድግ የስራ ዕድል በመፍጠር በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያስችል የስራና ተግባር ትምህርት የመስጠት ዓላማ አለው።
በውይይት መድረኩ በቢሮ ሀላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ስልጠናና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ ባሰሙት ንግግር የስልጠናው መርሀ ግብር የትምህርት ስርዓቱን ስብራት በመጠገን በቴክኒካል ክህሎቱ የዳበረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለውም ሁለቱ ተቋማት ያለቸውን ፀጋዎች በመለየት እና በጋራ በመስራት ሀገር የሚያሻግር ዜጋ መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የስልጠናው መርሀ ግብር የሀገሪቱን የመልማት ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ገበያ መር እንዲሆን ከማድረግ አንፃር በጥናት እየተለየ የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው የስልጠናው መርሀ ግብር ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን ትምህርት በተግባራዊ ልምምድ አዳብረው የሙያ ባለቤት እንዲሆን ከማድረግ አንፃር የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
በዚህም በ70/30 መርህ የትምህርት ቤት ላቦራቶሪዎችን ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችን የማሰልጠን አቅም ባገናዘበ መልኩ ተማሪዎችን በመደልደል ስራው እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ሀሳብና አስተያየት የስልጠናው መርሀ ተማሪዎች እንደየ ዝንባሌያቸው ከንድፈ ሀሳብ በዘለለ ክህሎት እንዲጨብጡ በማስቻል በገበያ ተፈላጊ የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ምቹ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
በአፈፃፀም መመሪያው መሰረት ስልጠናውን ለማስቀጠል ዘጠኝ አማራጮች ተለይተው የቀረቡ ሲሆን ነባራዊ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ ለመተግበር መግባባት ላይ ተደርሷል።
.