Welcome to AATVETB College
Announcement ተኪ ቴክኖሎጂዎች ለኢንዱስትሪ ምርታማነት" የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ በደመቀ ሁኔታ ቀጥሏል።

ተኪ ቴክኖሎጂዎች ለኢንዱስትሪ ምርታማነት" የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ በደመቀ ሁኔታ ቀጥሏል።

02nd May, 2026

ተኪ ቴክኖሎጂዎች ለኢንዱስትሪ ምርታማነት" የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ በደመቀ ሁኔታ ቀጥሏል።

🇪🇹አዲስ አበባ | ሚያዝያ 22/ 2018 ዓ.ም🇪🇹

በምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ "የቴክኖሎጂ ልዕቀት ለአገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ የሚገኘው 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽንና የፓናል ውይይት፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀጥሏል። 

በዕለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮርና ተቋማት ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ፤ የቴክኒክና ሙያ ዋነኛ ግብ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅና ወደ ገበያ ማቅረብ መሆኑን ገልጸዋል።

✍️ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችና የገበያ ትስስር

ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ በንግግራቸው እንደገለጹት፤ ቴክኒክና ሙያ ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ፣ መቅዳትና ማምረት ዋነኛው ነው። በአውደ-ርዕዩ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች በእሴት ሰንሰለት ተጠንተው ለኢንተርፕራይዞች የሚቀርቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በቀጥታ ወደ ተግባር የሚገቡና ለኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማትም እነዚህን ውጤቶች በመግዛት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።አሁን የቀረቡት የምርት፣ የማምረቻና የአይሲቲ መሠረት ልማት ቴክኖሎጂዎች ለኢንተርፕራይዞች ሲሸጋገሩ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩና የውጭ ምርቶችን የሚተኩ (Import Substitute) መሆናቸውን ወይዘሮ ዳግማዊት አክለው ገልጸዋል።

✍️ የክህሎት መናኸሪያና የፈጠራ ማዕከል

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ በበኩላቸው፤ ቴክኒክና ሙያ የእውቀት ባለቤት ብቻ ሳይሆን የክህሎት መናኸሪያና የትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መፈልፈያ መሆኑን ገልጸዋል። ዘርፉ ዛሬ የተለየ ተሰጥዖና የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ዜጎች ተሰባስበው ለሐሳባቸው ሕይወት የሚዘሩበት ተቋም መሆኑንም አረጋግጠዋል። በአውደ-ርዕዩ የቀረቡት ውጤቶች "የመርካቶ ውጤት ሳይሆኑ የሠልጣኝና የአሰልጣኝ የእጅ ሥራ ውጤቶች" መሆናቸውንም በኩራት ገልጸዋል።  

✍️ ተግባር-ተኮር ስልጠና ለቴክኖሎጂ ሽግግር

የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ዮሃንስ ሁንዴማ እንደገለጹት፤ ኤግዚቢሽኑ ሰልጣኞች በንድፈ-ሐሳብ የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚፈቱበት መድረክ ነው። መርሃ-ግብሩ የሰልጣኞችን ክህሎት በውጤት-ተኮር ስልጠና ከመገንባት ባለፈ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን ወደ እውነተኛ ሥራ በመቀየር "አምራች የቴክኒክና ሙያ ተቋም" የመሆን ራዕይን እውን ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመልክቷል። 

✍️  ማጠቃለያ፦

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ፣ ከ700 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ከ150 በላይ የኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጆች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ይህ ንቅናቄ ክህሎት መር የቴክኖሎጂ ፈጠራን በማሳደግ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ዳግም ያረጋገጠ ሆኗል።

.

Copyright © All rights reserved.