Welcome to AATVETB College
Announcement ከጥቃቅን ወደ ማሽን አምራችነትና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፡ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር የኢንተርፕራይዞችን ሕይወት እያሻሻለ ነው

ከጥቃቅን ወደ ማሽን አምራችነትና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፡ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር የኢንተርፕራይዞችን ሕይወት እያሻሻለ ነው

21st May, 2026

ከጥቃቅን ወደ ማሽን አምራችነትና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፡ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር የኢንተርፕራይዞችን ሕይወት እያሻሻለ ነው

ግንቦት 12/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ (ቲቪቲ) ዘርፍን የሀገራዊ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ሞተር ለማድረግ ስትራቴጂን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ ምሰሶ ደግሞ ስልጠናን ከገበያ ፍላጎት፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ከተግባራዊ ኢንተርፕራይዝ ድጋፍ ጋር ማጣመር ነው። ይህንን ሀገራዊ ራዕይ መሬት ላይ በማውረድ ረገድ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ እያከናወነ ያለው ተግባር፣ ስልጠናን ከተጨባጭ ውጤት ጋር በማገናኘት ለዘርፉ ትልቅ ማሳያ መሆን ችሏል።

የኮሌጁ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ምክትል ዲን አቶ ታከለ ኩሙላ እንደገለጹት፤ ኮሌጃቸው የቴክኖሎጂ ሽግግርን (Fabrication Engineering) በቀጥታ ከኢንዱስትሪዎች እና ከኢንተርፕራይዞች ተጨባጭ ፍላጎት (Need Assessment) በመነሳት ይጀምራል። በዚህ ስልት በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ 10 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሰርቶ ማሸጋገር የተቻለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በጨርቃጨርቅ አምራቾች ከፍተኛ ፍላጎት የተጠየቀውና ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት የተሸጋገረው "የእርም ደብሊንግ እና ሮሊንግ ማሽን (Yarn Doubling & Rolling Machine)" ይገኝበታል።

ኮሌጁ ባደረገው የውጤት ዳሰሳ ጥናት ባለፈው ዓመት የተሸጋገሩ ቴክኖሎጂዎች ብቻ በኢንተርፕራይዞች እጅ ላይ 749 ሺህ ብር የሚጠጋ አዲስ ሀብት ማፍራት የቻሉ ሲሆን፣ ይህንን አሃዝ እስከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ድረስ ወደ 1 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

ከምረቃ ወደ ቀጥታ ኢንኩቤሽን የወጣት ቆንጅት ተሞክሮ
የማርሽ ቀያሪው ምዕራፍ አንዱ ትልቁ ግብ ሰልጣኞች ተመርቀው ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ፣ ይልቁንም የስራ ፈጣሪነት ስነ-ልቦና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆነው የኮሌጁ የ2016 ዓ.ም የ"ኩሊናሪ አርት" (Culinary Arts) ተመራቂ የሆነችው ወጣት ቆንጅት ደግፊና የጓደኞቿ ስኬት ነው።
ወጣት ቆንጅትና ጓደኞቿ ከተመረቁ ማግስት ስራ ፍለጋ ከመንከራተት ይልቅ በኮሌጁ በኩል መነሻ ቁሳቁሶችን በማግኘት በግቢው ውስጥ የካፌ ስራ ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ አቋቁመዋል። ወጣት ቆንጅት ስታስረዳ፦ "ይህ እድል ከምንም በላይ ከቅጥር አድኖናል፤ በዚህ ወጣት እድሜያችን የራሳችንን ስራ በራሳችን ማስተዳደር እንድንችል አድርጎናል" ትላለች። በ35 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረው ይህ የተማሪዎች ካፌ፣ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ 70 ሺህ ብር ያሳደገ ሲሆን፣ ወደፊት ትልቅ ሆቴልና ሬስቶራንት በመክፈት ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አልመው እየሰሩ ይገኛል።

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ እና የምርት ማሳደግ ስኬት (የጀሚላ ሳሊም እና ኤደን ውብሸት ምስክርነት)
ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 859 ኢንተርፕራይዞችን በይዘት ለይቶ እየደገፈ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ 243 የሚሆኑት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍን (የካይዘን ስልጠና፣ የቢዝነስ ማኔጅመንት እና የማርኬቲንግ እውቀትን) በየሳምንቱ በተከታታይ ያገኛሉ። ለዚህ የረጅም ጊዜ ድጋፍ ማሳያ የሚሆኑትና ዛሬ ላይ ወደ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩት እንደ "ሳሚና ጀሚል" (የጀሚላ ሳሊም ጋርመንት) የተሰኙ ተቋማት ናቸው።

ባለሀብቷ ወጣት ጀሚላ ሳሊም እንደገለጹት፤ ከአስር አመት በፊት ከቤት ውስጥ ስራ በአንድ ማኑዋል ማሽን ሲጀምሩ ወረዳዉ ጥቃቅን ቦታዎችን በማመቻቸት የደገፈን ሲሆን ፣ኮሌጁ ተከታታይ የፓተርን ዲዛይን ቴክኖሎጂ ሽግግርና የካይዘን ስልጠናዎችን ሰጥቷቸዋል። በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ ከ40 በላይ ዘመናዊ ማሽኖችንና ከ20 በላይ ሰራተኞችን የያዘ ትልቅ የጋርመንት ኢንዱስትሪ ባለቤት መሆን ችለዋል።

የኮሌጁ ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ "የማርሽ ቀያሪው ምዕራፍ" ስትራቴጂ መሬት ላይ ሲወርድ ሀገራዊ ምርትን ማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬን መተካት እና የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት መቅረፍ ይቻላል። ክፍተቶቹን በቅንጅት በመፍታት ይህንን የልህቀት ተሞክሮ በሁሉም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ ማስፋፋት የነገ የማይባል የቤት ስራ ነው። አዘጋጅቼ ያቀረብኩላችሁ ተክለማርያም ጃታና ስሆን ቀጣይ በሌሎችም ዘርፎች ኮሌጁ ስትራቴጂዉን እንዴት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ በክፍል ሁለት ይጠብቁን፡፡ Like & share በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ፡፡

.

Copyright © All rights reserved.