Welcome to
Announcement ቴክኖሎጂ ለአመለካከት ሽግግርና ለኢንዱስትሪ መነቃቃት"፤ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶቹን ለእይታ አቀረበ።

ቴክኖሎጂ ለአመለካከት ሽግግርና ለኢንዱስትሪ መነቃቃት"፤ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶቹን ለእይታ አቀረበ።

24th April, 2026

ቴክኖሎጂ ለአመለካከት ሽግግርና ለኢንዱስትሪ መነቃቃት"፤ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶቹን ለእይታ አቀረበ። 

አዲስ አበባ | ሚያዝያ 16/ 2018 ዓ.ም

"ቴክኖሎጂ ልህቀት ለአገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ የሚገኘው 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አካል የሆነው የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን፣ በልደታ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ በድምቀት ተካሂዷል። ኮሌጁ በማምረቻ፣ በአገልግሎትና በአይሲቲ (ICT) ዘርፎች በአሰልጣኞችና ሰልጣኞች ጥምረት የተፈበረኩ 10 ያህል ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ለኢንዱስትሪዎች፣ ለኢንተርፕራይዞችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ለእይታ አቅርቧል። 

የአመለካከት ለውጥ ለዘርፉ ዕድገት - አቶ ተኩ ታዬ

የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ተኩ ታዬ የአውደ-ርዕዩን ፋይዳ አስመልክተው በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ እንዲህ ያሉ መድረኮች በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ቴክኒክና ሙያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ዲኑ እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኅብረተሰቡ አመለካከት እየተሻሻለ ቢመጣም፣ አሁንም ዘርፉን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ "ጫፍ የረገጡ" አመለካከቶች በሚፈለገው ልክ አልተቀየሩም። 

"በየዓመቱ እንዲህ ያሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አውደ-ርዕዮችን የምናዘጋጀው ኅብረተሰቡ በዘርፉ ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሰፋና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት የብልጽግና መሠረት መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው" ብለዋል አቶ ተኩ ታዬ። 

አክለውም፣ ቴክኖሎጂዎቹ በሰልጣኞች የተሠሩ መሆናቸውን ኢንዱስትሪዎች ሲረዱ፣ በሰልጣኞቻችን አቅም ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምርና ነገ ለሚጫወቱት ታላቅ ሀገራዊ ሚና መንገድ እንደሚከፍትላቸው ዲኑ በዝርዝር አስረድተዋል። 

"ክህሎት ከዳቦ በላይ ነው"፦ ተግባራዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር

በአውደ-ርዕዩ ላይ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርት "ከዳቦ በላይ" ለኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑን ያረጋገጡ ናቸው። 

ወደ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ (Standardization) የሚደረግ ጉዞ፦ 

ኮሌጁ አገልግሎቱንና ስልጠናውን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግና ጥራቱን ለማረጋገጥ የ ISO 21001:2018 የጥራት ማኔጅመንት ሥርዓትን ለመተግበር ላለፈው አንድ ዓመት ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም ራሱን በዛ ደረጃ ለማሻሻል በቀጣይነት እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል። በተለይ በጋርመንትና ሌዘር ዘርፍ የገበያ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ (Value Chain) ጥናቶች ተጠንተው ለኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተደረገ ይገኛል። 

የማኑፋክቸሪንግ ልህቀት፦ የብረት ማኑፋክቸሪንግ ባለሙያው ገመዳ ግርማ በበኩላቸው፤ የከበሩ ማዕድናትን የሚቆርጥ ማሽን፣ በአንድ ጊዜ 4 ብሎኬቶችን የሚያመርት ባለ ብዙ ሞልድ ማሽን እና የከብቶች እበትን በማቀነባበር ለባዮ-ጋዝ ሃይል ምንጭነት የሚቀይር ቴክኖሎጂ አቅርበዋል። 

የምግብ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ፦ አሰልጣኝ ሚሊዮን ወርቅነህ የሰው እጅ ንክኪ የሌለበትና ከውጭ የሚገባውን ከፍተኛ ወጪ የሚቀንስ የ"ኦቾሎኒ ቅቤ ማቀነባበሪያ" (Peanut Butter Processing Machine) ፈብርከው አቅርበዋል። ማሽኑ ወደ ምርት እንዲገባ ከኮሌጁ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ይገኛል። 

የፈጠራ ውጤቶች በቁጥር፦ ከማምረቻ እስከ ዲጂታላይዜሽን በኤግዚቢሽኑ ላይ በአጠቃላይ 10 የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 4 የማምረቻ፣ 4 የምርት እና 2 የአይሲቲ (ICT) ቴክኖሎጂዎች ይገኙበታል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተቋማዊ አሠራርን ከማዘመን ባለፈ ኢንዱስትሪዎችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ትልቅ አቅም ያላቸው ናቸው። 

የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ያሳየው ይህ የቴክኖሎጂ ንቅናቄ፣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ወደ አዲስ የልህቀት ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው። ኮሌጁ የፈጠራ ውጤቶቹ ወደ ሰፊ ምርት እንዲሸጋገሩና የሰልጣኞቹ አቅም በኢንዱስትሪው ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል። 

.

Copyright © All rights reserved.