ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ በማግኘትና በማስቀጠል፤ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በተቋማዊ ሥርዓት ግንባታ ያመጡት ስኬት፡፡
መጋቢት 9/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት የሥልጠና ተቋማቱን አደረጃጀትና አሠራር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
ይህ ተቋማዊ የለውጥ ጉዞ በዋናነት የሥልጠና ጥራትን ማረጋገጥና ሰልጣኞች በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ውስጥ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያለመ ነው።
የዚህ ጥረት አንኳር ማሳያ ደግሞ ተቋማቱ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን አሟልተው እንዲገኙ መደረጉ ሲሆን ይህም በከተማዋ የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ይህንን የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸው ተቋማቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባለፈ ለሰልጣኞች ልዩ ዕድልን በማጎናጸፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ትልቅ በር ከፍቷል።
የዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ 9001/2015 ዓለም አቀፍ የጥራት ስራ አመራር ሰርተፍኬት ባለቤት የሆነው የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ መለሰ ይግዛው እንደገለጹት የአይሶ ዕውቅና መገኘቱ ተቋሙ ካለው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለፈ ከጀርመን፣ ኬንያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር ጠንካራ የሥራ ትስስር እንዲፈጥር አስችሏል።
በተለይም ከኬንያው ሜሩ ኮሌጅ ጋር በተደረገው የጋራ መግባባት ሰልጣኞች ስልጠናቸውን በመከታተል የምስክር ወረቀት ያገኙ ሲሆን በሁለቱም ሀገራት የመሥራት ዕድል እንዳገኙ ጠቁመዋል፡፡
ከጀርመን ኮንስትራክሽን አሶሴሽን ጋር በተደረገ ትስስር መሰረት ደግሞ አሰልጣኞች በጀርመን ሀገር ሥልጠና ወስደው በቀጥታ ጀርመን ሀገር ሄደው የሚሰሩበት አሰራር መመቻቸቱን ገልጸዋል።
ተቋሙ አሰራሩን በማዘመኑ የተማሪዎች ቁጥር መጨመሩንና ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት የአይሶ ዕውቅናውን ማደሱን አቶ መለሰ አክለው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ 21001፡2018 የትምህርት ተቋም አስተዳደር ስርአት ማረጋገጫ ባለቤት የሆነው የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ሸለማ ንጉሱ በበኩላቸው አይሶ ለተቋሙ ትልቅ ዝና እና በኢንዱስትሪዎች ዘንድ ከፍተኛ እምነትን ማትረፉን አብራርተዋል።
ተቋሙ አጋር ፍለጋ መሄድ ሳያስፈልገው የውጭ ኩባንያዎች ራሳቸው በመምጣት አጋር ለመሆን ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን የጠቀሱት ዲኑ ይህም ሰልጣኞች በቀጥታ እንዲቀጠሩ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የአይሶ ስታንዳርድ አተገባበር መረጃዎችን በወጥ መንገድ ለመያዝ እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትልቅ ሚና መጫወቱን የገለጹት አቶ ሸለማ ተቋሙ ጥራቱን ለማስጠበቅ በየዓመቱ የሰርቪላንስ ኦዲት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በቅርቡ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ 21001፡2025 የትምህርት ተቋም አስተዳደር ስርአት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ባለቤት የሆነው የምርታማነት ማሻሻያና የልህቀት ማዕከል ዋና ዲን አቶ አድማሱ በቀለ እንደሚገልጹት ከሆነ የአይሶ ስታንዳርድ አተገባበር መጀመሪያ ላይ ልፋት ቢኖረውም አንዴ ከተገበረ በኋላ ግን ራሱን የቻለ ዘላቂ ተቋማዊ ሥርዓት እንደሚገነባ አስረድተዋል።
በተለይም በዲጂታል አሠራር ላይ በማተኮር የተገነባው ሥርዓት ሰልጣኞች በሀገር ውስጥም ሆነ እንደ ናይሮቢና ባሉ የጎረቤት ሀገራት ከተሞች እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ስታንዳርዱ በመጀመሪያ እንደ አስገዳጅነት ቢቀመጥም አሁን ላይ ግን ሰራተኛው አሰራሩን የራሱ ማድረጉንና ተቋሙን ሁልጊዜም ለውድድር ዝግጁ እንዲሆን ማድረጉን አቶ አድማሱ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ሥልጠና ተቋማት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ እንደገለጹት ቢሮው የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ጥራት ለማረጋገጥ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን እንደ ዋነኛ ስትራቴጂ ይዞ እየሠራ ይገኛል።
ተቋማቱ የአሠራር ለውጥ የሚያመጣ ግልጽነትን የሚፈጥርና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሥርዓት መሆኑን በመረዳት በራሳቸው ተነሳሽነት እየተገበሩት እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ይህ አሠራር ሰልጣኞችን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለአውሮፓና ለአረብ ሀገራት ጭምር ለሚሆን ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ለማቅረብ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የጠቆሙት ኃላፊዋ አንድ ሰልጣኝ በአይሶ ዕውቅና ባለው ተቋም ሰልጥኖ ሲወጣ የሚያገኘው የምስክር ወረቀት በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቀባይነት እንዲኖረው አጋዥ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
በቀጣይም ሁሉም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ይህንን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ተከትለው በመሥራት የሥልጠና ጥራታቸውን እንዲያሳድጉና ለኢኮኖሚው የሚመጥን ብቁ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

.