የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከንድፈ-ሃሳብ ወደ ተግባር ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡
መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አማካኝነት በለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የተካሄደው የ16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት <<የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለሀገር ኢኮኖሚ ምጥቀትና ብልፅግና>> በሚል መሪ ቃል የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና የቴክኖሎጂ ሽግግር መርሃ ግብር የዘርፉን አዲስ ምዕራፍ ያበሰረ ሆኖ ተካሂዷል።
ያደጉ ሀገራት የፈጣን እድገት ሚስጥራቸው ሙያን ማክበርና ቴክኖሎጂን በየጊዜው ማሻሻል መሆኑን በመጥቀስ መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ቴክኖሎጂ ከቁሳቁስ ባለፈ የሰውን አመለካከትና ሰርቶ የመለወጥ ትጋትን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም ኮሌጆቻችን ቴክኖሎጂን ከመቅዳትና ከማላመድ ባለፈ ወደ መፍጠር በመሸጋገራቸው የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ትልቅ አቅም እየፈጠሩ መሆኑንና ይህም በተጨባጭ የማህበረሰቡን ህይወት የሚቀይር መሆኑን አስገንዝበዋል።
የቢሮው የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች የሚፈልቁበትና የኢንተርፕራይዞችን ምርታማነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች ለገበያ የሚቀርቡበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ መርሃ ግብር ሰልጣኞች፣ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪዎች የኮሌጆችን አቅም በመጠቀም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ተግባራዊ ስራዎችን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩበት ወቅት መሆኑንም አብራርተዋል።
በሳምንቱ ውስጥ የክህሎትና የጥናት ምርምር ውድድሮች እንዲሁም የፋሽን ሾው ኩነቶች መከናወናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው መርሃ ግብሩ ለከተማዋ ትርፋማ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ጎልተው የሚወጡበት መሆኑን አስገንዝበዋል። እውቀትን ወደ አንድነት በማምጣት ለሀገር የሚተርፍ ስራ የመስራት ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ በማቅረብ በጋራ በመቆም የሀገርን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተቋሙ ብቁ ባለሙያዎችን ለኢንዱስትሪው ከመደበኛና ከአጭር ጊዜ ስልጠናዎች ባለፈ አሰልጣኞች ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቀጥተኛ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የጠቀሱት የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ዋና ዲን ዶ/ር ታደሰ መኮንን በአሁኑ ወቅት ከ1,500 በላይ ኢንተርፕራይዞች ከኮሌጁ ድጋፍ እያገኙ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂም ፈጠራን ያከሉ ቴክኖሎጂዎች በቀጥታ ወደ መሬት እንዲወርዱና የውጭ ምንዛሬን እንዲቀንሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለጹት ዋና ዲኑ ኮሌጁ የራሱ ኢንተርፕራይዝ እንዳለውና እንደ ስማርት ፖል ያሉ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረበውና በኢንተርፕራይዞች ዘንድ ያለውን ክፍተት መሰረት ያደረገው የሳሙናና የላርጎ ማቀናበሪያ ቴክኖሎጂ ትኩረት የሳበ ፈጠራ ነበር። ይህ ተንሸራታች ሞተር ያለው ማሽን የሰራተኛ ቁጥርን የሚቀንስ ጊዜን የሚቆጥብና የምርት ጥራትን የሚጨምር መሆኑን የገለጹት የኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት አሰልጣኝ ጴጥሮስ መጃ ቴክኖሎጂዎች ወርክሾፕ ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ እንደዚህ አይነት ችግር ፈቺ ስራዎች ወደ መሬት ወርደው ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ ኮፒ በመደረጉ የውጭ ምንዛሬን በማዳንና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ያለውን ፋይዳ አሰልጣኙ አስረድተዋል።
ቀደም ሲል ቴክኖሎጂው መሬት ላይ የወረደ ባለመሆኑ ለኢንተርፕራይዞች አስቸጋሪ እንደነበር በማስታወስ ምስክርነታቸውን የሰጡት የነጻነት ሳህለእግዜርና ጓደኞቻቸው ሳሙና ማምረቻና መሸጫ ኢንተርፕራይዝ ኃላፊ አቶ አማኑኤል በላይ ናቸው።
አሁን ግን ኮሌጁ የፈሳሽ ጽዳት እቃዎች ማምረቻ ማሽንን ለኢንተርፕራይዙ በማስተላለፉ የሰው ኃይልን ጊዜንና ወጪን የሚቀንሱ ስራዎችን በመስራቱ ለኢንተርፕራይዛቸው ትልቅ እረፍት መሆኑን ጠቅሰው የሚሰራ አካልና የሚቀበል አካል በመገናኘታቸው ቴክኖሎጂው ወደ መሬት ወርዷል በማለት የኮሌጁና የኢንተርፕራይዞች ትስስር ሀገርን ወደመጥቀም ደረጃ መሸጋገሩን አረጋግጠዋል።
በአውደ ርዕዩ ከቴክኖሎጂ ሽግግር በተጨማሪ የፋሽን ሾው ውድድርና የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
.