Welcome to AATVETB College
Announcement የኢንዱስትሪ አብዮትና የሰው ልጅ ወደ ማሽንነት የተቀየረበት ጥቁር ዘመን።

የኢንዱስትሪ አብዮትና የሰው ልጅ ወደ ማሽንነት የተቀየረበት ጥቁር ዘመን።

02nd May, 2026

የኢንዱስትሪ አብዮትና የሰው ልጅ ወደ ማሽንነት የተቀየረበት ጥቁር ዘመን።

ከ140 ዓመታት በፊት የተከሰተው የኢንዱስትሪ አብዮት ለዓለም አዲስ የቴክኖሎጂ ብርሃን ይዞ የመጣ ቢመስልም፣ በስተጀርባው ግን በታሪክ የማይረሳ ሰብዓዊ ስቃይን አዝሎ ነበር። 

በወቅቱ የነበረው የካፒታሊዝም ሥርዓት ሰራተኛውን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አንዱ የፋብሪካ ማሽን ይቆጥረው ነበር። ሠራተኞች ከማለዳው 11 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 4 ሰዓት ድረስ ለ16 ሰዓታት ያለ እረፍት እንዲሠሩ ይገደዱ ነበር።

 በተለይም ሕፃናት በትምህርት ገበታ ፋንታ በፋብሪካ ጭስ ውስጥ እንዲታፈኑ መደረጋቸውና እናቶች ያለምንም የወሊድ ፈቃድ በቆሙበት እንዲወልዱ መገደዳቸው የዘመኑን እጅግ አሰቃቂ ገጽታ ያሳያል። ይህ "ጥቁር ህልም" የሰው ልጅ ሰብዓዊነት ክብር የወደቀበትና ጉልበት በግፍ የሚበዘበዝበት ወቅት ነበር።

የቺካጎው ትግልና የመብት ማስከበር መስዋዕትነት

ይህ መጠነ ሰፊ ግፍና በደል የወለደው መራራ ትግል በ1886 (እ.ኤ.አ) በቺካጎ ከተማ ፈነዳ። ሠራተኞች "እኛ ማሽን አይደለንም፣ ሰው ነን!" በሚል ጽኑ ድምፅ አደባባይ ወጡ። "8 ሰዓት ለሥራ፣ 8 ሰዓት ለዕረፍት፣ 8 ሰዓት ለእንቅልፍ" የሚለው ታሪካዊ ጥያቄ የዛሬው ዓለም አቀፍ የሥራ መመሪያ መሠረት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጥያቄ በቀላሉ አልተመለሰም፤ የሠራተኞች ደም ፈሷል፣ በጠመንጃ ጥይት ተቆልተዋል፣ ብዙዎችም በአደባባይ ተሰቅለዋል።

 ዛሬ የምናገኘው የሳምንት ዕረፍት፣ የወሊድ ፈቃድ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያና የሥራ ቦታ ደህንነት መብቶች በሙሉ በነዚያ ጀግኖች ደምና አጥንት የተገነቡ እንጂ በነፃ የተገኙ ስጦታዎች አይደሉም።

የስራና ክህሎት ቢሮ ተልዕኮ፦ ሰብዓዊነትን የተላበሰ የስራ አካባቢ

በኢትዮጵያም ሆነ በከተማችን አዲስ አበባ፣ የሥራና ክህሎት ቢሮ የተቋቋመው እነዚህን በደም የመጡ የሠራተኛ መብቶችን ለማስከበርና ለዜጎች ምቹ የሥራ ሁኔታን ለመፍጠር ነው። 

የቢሮው ተልዕኮ ዜጎች በክህሎት የበለፀጉና በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማብቃት ብቻ ሳይሆን፣ የሠራተኛውና የአሠሪው ግንኙነት በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ማድረግ ነው። ቢሮው የሥራ ቦታ ደህንነትን በማረጋገጥ፣ ተገቢውን የሥራ ሰዓትና ክፍያ በመከታተል፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሰላምን በማስፈን የሠራተኛውን ሰብዓዊ ክብር የመጠበቅ ታሪካዊ አደራ አለበት። ይህም ትላንት በቺካጎ የተጀመረውን የፍትህ ትግል በዘመናዊና በተቋማዊ መንገድ የማስቀጠል ሥራ ነው።

የክህሎት ልማት ለተሟላ የሠራተኛ ክብር

በዛሬው ዘመን የሠራተኛው ቀን ሲከበር ከመብት ጥያቄ ባሻገር "ክህሎትን" ማሳደግ የክብር መገለጫ ሆኗል። የሥራና ክህሎት ቢሮ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ በማሰልጠንና ብቁ በማድረግ፣ ሠራተኛው በጉልበቱ ብቻ ሳይሆን በዕውቀቱና በቴክኖሎጂ ታግዞ ራሱንና ሀገሩን እንዲለውጥ እየሠራ ይገኛል። 

ሚያዝያ 23 ስናከብር፣ በትላንትናው መስዋዕትነት የተገኘውን መብት እያከበርን፣ በዛሬው የክህሎት ልማት ደግሞ የሠራተኛውን ተወዳዳሪነትና ምርታማነት ለማረጋገጥ ቃል የምንገባበት ቀን ነው። የሠራተኛው ክብር የሚጠበቀው መብቱ ሲከበርና ለሥራው የሚመጥን ዕውቀትና ጥበብ ሲታጠቅ ብቻ በመሆኑ፣ ቢሮው ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን ይተጋል።

.

Copyright © All rights reserved.