ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመደገፍ የሚያስችል ኮምፒውተሮችን በስጦታ አበረከተ።
ታህሳስ 7/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመቀየር እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ የሚያስችል ስድስት ላፕቶፖችና አራት ኮምፒውተሮች ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ተበርክቶለታል።
በርክክቡ ስነ-ስርዓት ድርጅቱ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን የገለፁት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በቀጣይም የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን የማጠናከር ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ድርጅቱ ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን የገለፁት በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የስራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ በተለይም የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ለማጠናከር የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመስጠት ባሻገር በዛሬው ዕለትም 10 ኮምፒውተሮችን አበርክቷል ብለዋል።
በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የፍልሰት አስተዳደር ዩኒት ኃላፊ ተወካይ ነይሻ ሚካሪንጓ ስጦታውን ባበረከቱበት ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉ በስራ ዕድል ፈጠራ የሚከናወነውን ተግባር በማገዝ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ለማፈላለግ ያስችላል ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለውም ድርጅቱ የአቅም ግንባታ ስራውን በማጠናከር የአንድ ማዕከላትን ለማጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ቢሮው ዘመናዊ የአሰራር ዘዴዎችን በመጠቀም የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ለማጠናከር እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በቅርቡ በአንድ ጀምበር የሥራ ዕድል ፈጠራ ከ30ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በፍጠር በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ማሸጋገሩ የሚበረታታ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።
.