Welcome to
Announcement ጠንካራ የስራ ባህልን ያዳበረ ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጠንካራ የስራ ባህልን ያዳበረ ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

26th September, 2025

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአንድ ሀገር እድገትና ብልፅግና እውን መሆን በቴክኒክና ሙያ ጠንካራ የስራ ባህልን ያዳበረ ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል አሉ።

ከንቲባ አዳነች ይህን ያሉት የከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት ቢሮ በመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ 7 ሺህ 149 ሰልጣኞችን ባስመረቀበት ወቅት ነው።

ቢሮው በፍላጎት መር የስልጠና መርሐ ግብር ከደረጃ ሁለት እስከ ደረጃ አምስት ለቢሮው ተጠሪ በሆኑ 14 የመንግስት ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በ22 የስልጠና ዘርፎች ሰልጥነው ብቁ የሆኑ ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት የዛሬው ትውልድ ለነገው ትውልድ ስንቅ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅ ገልጸው÷ ይህን እውን ለማድረግ ጠንካራ የስራ ባህል ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎችን ችግር ፈቺ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ አዳዲስ የፈጠራ ስራ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ኮሪደርን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ የልማት ስራዎች የቴክኒክና ሙያ የስራ ውጤት የሆኑ ግብዓቶች በከፍተኛ ሁኔታ አገልግሎት ላይ መዋላቸውንም ገልጸዋል።

ከትምህርት በተጨማሪ በስራ ዓለም ሙያቸውን በማሳደግ ከሀገር ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መትጋትና መስራት ይኖርባችኋል ሲሉም ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ከተማ አስተዳደሩ ጥራትን ለማሳደግና ዘርፉን ይበልጥ ወደፊት ለማሻገር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

.

Copyright © All rights reserved.