Welcome to
Announcement ጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከGIZ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን ወጣቶች አስመረቀ ለተመራቂዎቹም የቀጥታ የስራ ትስስር ተፈጥሯል::

ጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከGIZ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን ወጣቶች አስመረቀ ለተመራቂዎቹም የቀጥታ የስራ ትስስር ተፈጥሯል::

23rd April, 2026

ጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከGIZ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን ወጣቶች አስመረቀ ለተመራቂዎቹም የቀጥታ የስራ ትስስር ተፈጥሯል::

ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ የከተማዋን ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶችን በክህሎት በማብቃትና የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የድጋፍ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

 ከዚህ ጋር ተያይዞም ጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (GIZ_QEP ምዕራፍ III IVC) ጋር በመተባበር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 107 ሰልጣኞች  አስመርቋል።

 በምረቃው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ አሁን የደረስንበት ዘመን የዲግሪ  መያዝ ብቻ   ሳይሆን ዜጎች በሰለጠኑበት  የሙያ መስክ ተሰማርተው ስራ በመፍጠር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዕድል የሚፈጥሩበት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

 ኃላፊው አክለውም እውነተኛ ስራ ፈጣሪነት ከአስተሳሰብና ከደንበኛ ፍላጎት የሚነሳ መሆኑን ጠቁመው እውቀት በተግባርና በእጅ ተለክቶ ወደ ስራ መተርጎም እንዳለበት አሳስበዋል።

የጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን ዶ/ር አሸብር ተክሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርጻ ወደ ተግባር መግባቷን አስታውሰዋል። 

የዚህ ፖሊሲ ዋነኛ አካል የሆነው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ወጣቱን ወደ ስራው ዓለም ለመቀላቀል የሚያስችል የክህሎት መር ስልጠና ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና  ዲኑ ኮሌጁ ይህንን ሀገራዊ ስትራቴጂ በተግባር ለመተርጎም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

 ኮሌጁ በገበያው ላይ ተፈላጊ የሆኑ የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ሰልጣኞች የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ ወይም በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው እንዲሰሩ ብቃታቸውን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንና የዕለቱ የምረቃና የስራ ትስስር መርሃ ግብርም የዚሁ ጥረት ውጤት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

በዕለቱ ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ስምንት ቀጣሪ ድርጅቶች በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም ቃለመጠይቅ በማድረግ የቀጥታ የስራ  ትስስር አድርገዋል። 

ይህ በኮሌጁ እና በጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ትብብር የተገኘው ውጤት ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆን ተግባር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ስልጠናው ወጣቶችን በክህሎት በማብቃትና ወደ ስራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማድረግ ረገድ ያለውን ሚና ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ አድንቀዋል።

.

Copyright © All rights reserved.