Welcome to
Home የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ ትግበራ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑ ተገለጸ፡

የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ ትግበራ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑ ተገለጸ፡

23rd February, 2026

የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ ትግበራ  በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የካቲት  14/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ  የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና   ጥራትን ለማረጋገጥና የበቃ ሰልጣኝ ለገበያው ለማቅረብ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚህም መካከል የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ ትግበራ በኮሌጆች የሰልጣኝ ቅበላና የስልጠና ጥራት ላይ መዋቅራዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።

ሪፎርሙ ከተተገበረባቸው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ደግሞ ጄኔራል ዊንጌት ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች ተጠቃሽ ናቸው።

ቀደም ሲል በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች የነበረው የሰልጣኝ ቅበላ አሰራር ያለገደብና አቅምን ያላገናዘበ እንደነበር የሚታወስ ነው። የጄኔራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ ጀቤሳ ሙለታ እንደሚገልጹት አዲሱ ስትራቴጂ ይህንን አካሄድ በጥናትና በእቅድ እንዲተካ አድርጎታል። ከዚህ ቀደም ሰልጣኝ ቅበላው ትኩረት ሲያደርግ የነበረው ብዛት ላይ እንደ ነበር አሁን ግን ጥራት ላይ ትኩረቱን  አድርጓል ይላሉ።

በዚህ መሠረት ጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዘንድሮ የቀን፣ የማታና የቅዳሜና እሁድ ፕሮግራሞችን ጨምሮ 3,638 አዳዲስ ሰልጣኞችን የተቀበለ ሲሆን በአጠቃላይ 6,571 ሰልጣኞች በግቢው ውስጥ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። ይህ ቁጥር ከኮሌጁ የመቀበል አቅም ጋር የተመጣጠነ ሲሆን ከአቅም በላይ የሆኑ ሰልጣኞች አሰራርን በጠበቀ መልኩ ወደ ሌሎች ክላስተር ኮሌጆች እንዲሄዱ ተደርጓል። በተመሳሳይ በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኮሌጅ አጠቃላይ የሰልጣኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረበት 530 ወደ 1,066 በማደግ የ100 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የስትራቴጂው መተግበር  በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ውጤታማ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት የኮሌጁ ስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን  አቶ ረመዳን አብዱረህማን በተለይም የሰልጣኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል። ይህ ለውጥ የመጣው ኮሌጆች በክላስተር ተደራጅተው ሙያዎችን ተደራሽ እንዲያደርጉ በጥናት ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ በተደረገው የዞኒንግ ስትራቴጂ አማካኝነት እንደሆነ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ስትራቴጂው የስልጠና ጥራትን ለማሻሻልና ግብአቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። ኮሌጁ ስፔሻላይዝ እንዲያደርግባቸው በተለዩት እንደ ጋርመንትና ሌዘር፣ ሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም አውቶሞቲቭ ባሉ ዘርፎች ላይ ብቻ በጀቱን በማዋል ማሽነሪዎችንና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማሟላት አስችሏል። በተጨማሪም በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት ብቁ አሰልጣኞች እንዲመደቡ መደረጉ አሰልጣኞች በሰልጣኞች ውጤት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩና ጥራቱ እንዲጠበቅ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህ የታችኛው መዋቅር ለውጥ በተግባር የታየው በጄኔራል ዊንጌት የከተማ ግብርና አሰልጣኝ የሆኑት አቶ አየለ ብርሃኑ በሚሰጡት ምስክርነት ነው። አቶ አየለ እንደሚገልጹት ቀደም ሲል የነበረው የሰልጣኝ ቁጥር ብዛት ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት ፈታኝ ነበር። 

አሁን ላይ ለአንድ ክፍል  25 ሰልጣኝ ሁለት አሰልጣኞች እንዲመደቡ በመደረጉ አሰልጣኙ በቂ የዝግጅት ጊዜ አግኝቶ እንዲያሰለጥን አስችሎታል። እንዲሁም የሰልጣኝ እና የአሰልጣኝ ቁጥር በመመጣጠኑ እውቀትን እና ክህሎትን ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ስትራቴጂው ከሰልጣኞች ቅበላ ባለፈ በጀትን በውጤታማነት ለመጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። አቶ አየለ ብርሃኑ እንደሚገልጹት  ቀደም ሲል በርካታ የስልጠና ዘርፎች በአንድ ላይ ይሰጡ ስለነበር የግብዓት መበታተን ይስተዋል የነበረ ሲሆን  ይህም በስልጠና ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው። አሁን ግን ኮሌጁ ያለውን ፋይናንስና በጀት ተለይተው ስፔሻላይዝ በሚደረግባቸው ዲፓርትመንቶች ላይ ብቻ በማዋሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ሙሉ ለሙሉ ማሟላት ተችሏል።

ይህ አሰራር ለስልጠና የሚፈለጉ ግብዓቶችን  በቀላሉ እንዲገኙ በማድረግ የአሰልጣኙን የስራ ጫና ከመቀነሱም በላይ ስልጠናውን በሙሉ ትኩረት እንዲመራ አግዞታል። በዚህም ሰልጣኞች በቂ ክህሎት እውቀትና ተገቢውን አመለካከት ይዘው እንዲወጡ ከማድረጉም ባለፈ በሀገር አቀፍ ምዘና ወቅት ያላቸውን የመብቃት ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ ያደርገዋል።

ምንም እንኳን የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን አሰራር የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም ውጤቱ ግን ተስፋ ሰጪ መሆኑን አመራሮቹና አሰልጣኞች ይስማማሉ። እንደ አቶ አየለ ገለጻ ይህ ስፔሻላይዝ የማድረግ ሂደት ኮሌጁን ብቻ ሳይሆን ሀገርን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ከሀገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ሰልጣኞችን ለማፍራት መሰረት ይጥላል።

የሪፎርሙን ሙሉ ውጤት በአንድ አመት ውስጥ ማየት ባይቻልም በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት አመታት ውስጥ ግን ተወዳዳሪ  እና ስራ ፈጣሪ የሆኑ ሰልጣኞችን እንደምናፈራ እርግጠኞች ነን ሲሉ አቶ ጀቤሳ ሙለታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

.

Copyright © All rights reserved.