አመራሩ በዘርፉ እሳቤዎቹ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለላቀ ውጤት መትጋት እንደሚገባው ተገለፀ።
ታህሳስ 9/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ በአዋጅ ቁጥር 84/2016 ከተቋቋሙ የከተማ አስተዳደሩ ቁልፍ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ቢሮው በ2022 ዓ.ም ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ምቹ የስራ ሁኔታ የተረጋገጠበት ዘላቂ የስራ ዕድል በከተማዋ የመፍጠር ራዕይ ሰንቆ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ራዕዩን ከግብ ለማድረስ ደግሞ በዘርፉ እሳቤ የጋራ ግንዛቤ ያለው አመራርና ሰራተኛ ለመፍጠር የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል በመስራት ላይም ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም ከማዕከል እስከ ወረዳ ላሉ የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም ለተጠሪ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲኖች በዘርፉ አዲሱ እሳቤ፣በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ የሽግግር እቅድና አፈፃፀም እንዲሁም በቢሮው የ10 ዓመታት ግቦች ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በስልጠናው መርሀ ግብር ባደረጉት ንግግር አመራሩ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ በማጤን እና የአመራር ጥበቡን በማሻሻል ለተቋማዊ ዕቅድ ስኬት መትጋት ይገባዋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ጠንካራ አደረጃጀቶችን በየደረጃው በመፍጠር እና በእሳቤዎቹ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለላቀ ውጤት መትጋት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ቢሮው የስራ ዕድል ፈጠራ ስራው ግምታዊ ሳይሆን ሳይንሳዊ ዘዴዎች በመከተል በጥናት የተደገፈ ከማድረግ አንፃር በርካታ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።
በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የስራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ የስልጠናው ርዕሶችን መሰረት አድርገው ባደረጉት ገለፃ ቢሮው በከተማዋ የሚስተዋለውን 27.7 በመቶ የስራ አጥ ምጣኔ ወደ ስምንት በመቶ ለማውረድ በጥናት የተደገፈ ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል።
የሥራ ዕድል ፈጠራው በክህሎት እንዲመራ በማድረግ ዘለቂ የስራ እድል ለመፍጠር ሥራ ፈላጊ ዜጎች በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በክህሎት ስልጠና እንዲያልፉ እየተደረገ ይገኛል።
በቀጣዮቹ ዓመታትም የሥራ ዕድል ፈጠራ ስራውን በማላቅ የ10 ዓመታት ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ እና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

.