Welcome to
Announcement የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የእርጎ ማርጊያ ማሽንን ጨምሮ ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል::

የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የእርጎ ማርጊያ ማሽንን ጨምሮ ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል::

27th April, 2026

የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የእርጎ ማርጊያ ማሽንን ጨምሮ ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል:: 

ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም 

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ከተለመደው የማሰልጠን ተግባር ባለፈ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠንና ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የሀገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። 

በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ  የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አዳዲስ ሪፎርሞችንና ስትራቴጂዎችን መሠረት በማድረግ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎትንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሥራው ዋነኛ አካል አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። 

ይህ ተግባር ኢንተርፕራይዞች በቴክኖሎጂ ታግዘው ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉና የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ እንዲተኩ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዲን አቶ ወንድምሲያምረኝ መኮንን እንደገለጹት ኮሌጁ በዞኒንግና ዲፈረንሼሽን  እሳቤ በስነ-ጥበብ ፣ በጋርመንት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሆቴል ዘርፎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። 

ኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን የሚያከናውነው በሥራና ክህሎት ቢሮ ደረጃ የተጠናውን የእሴት ሰንሰለት ትንተና የኢንተርፕራይዞችን ትክክለኛ የፍላጎት ዳሰሳ መሠረት በማድረግ ነው።

በዚህም ሂደት የውጭ አገር ምርቶችን  በመተካትና የሀገር ውስጥ አቅምን በማሳደግ ኢንተርፕራይዞች በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል። 

ለአብነትም በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥማቸውን የመኖ ውድነት ለመቅረፍ ኮሌጁ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን አምርቶ በማቅረብ ላይ ሲሆን ይህም ኢንተርፕራይዞቹ ከመኖ ግዥ ላይ የሚያወጡትን ወጪ ከ50 በመቶ በላይ እንዲቀንሱ ከመርዳቱም በላይ  በኮሌጁ ግቢ ውስጥ በሳምንት ከ6 ሺህ በላይ እንቁላል በማምረት በቅናሽ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ አስችሏል።

በኮሌጁ ከተከናወኑ ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች መካከል በወተት ምርትና ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ያደረገው "የእርጎ ማርጊያ ማሽን" በዋነኝነት ይጠቀሳል። 

የመላኩ ኢዮስያስና ጓደኞቻቸው ማህበር አባል የሆኑት አቶ ሳሙኤል መስፍን እንደመሰከሩት ማሽኑ ቀደም ሲል እስከ 6 ሰዓት ይፈጅ የነበረውን የማርገት ሂደት ወደ 3 ሰዓት ዝቅ በማድረግ የምርት ጥራትና ፍጥነትን ጨምሯል። 

ከዚህ በተጨማሪ ኮሌጁ በ21 ቀናት ውስጥ እስከ 1,500 እንቁላሎችን የመፈልፈል አቅም ያለው ማሽን፣ የጋራዦችን ሥራ የሚያፋጥን የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶችን ወደ ጥሬ ዕቃ የሚቀይር መሣሪያ እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎች በመኖሪያ ግቢያቸው የጓሮ አትክልቶችን እንዲያመርቱ የሚያስችል የ"ሃይድሮፖኒክ" ቴክኖሎጂን በማልማት ላይ ይገኛል።

በጠቃላይ በኮሌጁ እየተከናወኑ ያሉ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለኢንዱስትሪው ዕድገት ያላቸውን ፋይዳ በተግባር እያሳዩ ነው።

እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች ኢንተርፕራይዞች ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉ፣ ወጪያቸውን እንዲቀንሱና ጥራት ያለው ምርት ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ በማስቻል ረገድ የላቀ ሚና አላቸው። 

ወደፊትም ኮሌጁ ከኢንተርፕራይዞች ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ በማጠናከር የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጀርባ አጥንት እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ይጠበቃል።

.

Copyright © All rights reserved.