ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው መመሪያ መሰረት ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁለተኛው ዙር ተግባራዊ በሚደረጉት 11 የሥራና ተግባር ትምህርት የሙያ ዘርፍች እቅድ ላይ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ጋር ውይይት አካሄዳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ክቡር ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁለተኛው ዙር ተግባራዊ የሚደረጉ 11 የሥራና ተግባር ትምህርት የሙያ ዓይነቶችን የተመለከተ መመሪያ ማስተላለፍን ገልፀው ትምህርቱን ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል በተዘጋጀው እቅድ ላይ በመወያየት ተማሪዎችን ለማሰልጠንና ለማብቃት እንዲቻል መድረኩ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀላፊው አክለውም በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፓሊሲ ላይ የሙያና ቴክኖሎጂ ትምህርት ከተማሪዎች እድሜ ጋር የተመጣጠነ ሆኖ እንዲሰጥ የሚያስቀምጥ መሆኑን ጠቁመው በመጀመሪያ ዙር በ12 የሙያ የትምህርት ዘርፍች ላይ የሥራና ተግባር ትምህርት ከሌሎች ትምህርቶች ጋር ተቀናጅቶ እንዲሁም 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ራሱን ችሎ ተማሪዎች በቀጣይ የሚፈልጉትን ሙያ እንዲመርጡ በሚያስችል መልኩ እየተሰጠ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች የክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ ከስር መሰረቱ በመስራት አምራች ዜጋን ለመፍጠር በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ በቢሮ ሀላፊ ደረጃ የውጤት ተኮር ስልጠና እና የተቋም ልማት ዘርፍ ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ ሀገራዊ ፓሊሲን በመተግበር ትውልድ በመገንባት ለገበያው የበቃ የሰው ሀይል ለማቅረብ በቅንጅት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ አበራ እቅዱን ሳቀርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁለተኛው ዙር እንዲተገበሩ ለተለዩት 11 የሙያ አይነቶች ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል መርሐ ትምህርቶች እንዲሁም ለ11ኛ ክፍል የተማሪ ሞጁሎችና የመምህር መምሪያዎች ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀው በትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ የተገለፁ የ11 የሙያ አይነቶች ዝርዝርን ማለትም ብረታ ብረት ሥራ ቴክኖሎጂ ፣ አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ፣ አልባሳት ቴክኖሎጂ ፣ ህንፃ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋት ፣ ቧንቧ ስራ ፣ ሶፍትዌር ማበልጸግ ፣ ሰብል አመራረት ፣ ጤና ክብካቤ አገልግሎት ፣ ሆቴል አገልግሎት ፣ ፀጉር ሥራና ውበት አገልግሎት እንዲሁም ምግብ ዝግጅት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት እንዲሁም ስራና ክህሎት ቢሮዎች ስራ ሀላፊዎች እና በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ኮሌጆች ዲኖች መገኘታቸውን ከአዲስ አበባ ትምህር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
.