Welcome to
Announcement የከተማ አስተዳደሩ ለቴክኒክና ሙያ ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ባስመዘገባቸው ስኬቶች ለሌሎች ሀገራት አርአያ መሆን መቻሉ ተገለፀ።

የከተማ አስተዳደሩ ለቴክኒክና ሙያ ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ባስመዘገባቸው ስኬቶች ለሌሎች ሀገራት አርአያ መሆን መቻሉ ተገለፀ።

03rd September, 2025

በከተማዋ በቴክኒክና ሙያ ዘርፉ የተመዘገበውን  ለውጥ ተከትሎ የተለያዩ ዓለም ሀገራትን ቀልብ እየሳበ እና የተሞክሮ መቅሰሚያ ማዕከል እየሆነ መጥቷል።

ዘርፉ ባለፉት ዓመታት ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት  ማበርከት ከሚጠበቅበት አስተዋጽኦ አንፃር ሚናው አናሳ መሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዘርፉ በተካሄደው ሪፎርም ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ከመሆናቸውም ባሻገር ለተለያዩ  ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት ተሞክሮዎች በማጋራት ላይ ይገኛል።

በዛሬው  ዕለትም ከሌሴቶ፣ቦትስዋና  እና  ከደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበር የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ቡድን አባላት በጄኔራል ዊንጌት፣ በምስራቅ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንዲሁም በኢንተርፕራይዞች የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

ልዑክ ቡድኑ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችና በኢንተርፕራይዞች ባደረገው የስራ ጉብኝት የትምህርትና ስልጠና ስርዓቱን በአዲሱ የዘርፉ  እሳቤ በመቃኘት ገበያ መር ሥልጠና በመስጠት ሂደት እያከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተመልክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ባስመዘገባቸው ስኬቶች ለሌሎች ሀገራት አርዓያ እየሆነ መጥቷል ያሉት በቢሮ ሀላፊ ደረጃ  የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ  የውጤት ተኮር ስልጠናና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ  ጉብኝቱ   የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ለከተማዋ ዕድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ  ማሳያ ነው ብለዋል።

ተቋማቱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ እየሰራ ባለው ስራ ጄኔራል ዊንጌት ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ የልህቀት ማዕከል በማቋቋም ቀጠናዊ ትብብርን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

መቀመጫውን ሌሴቶ  ያደረገው የጀርመን መንግሥት የልማት ተራድኦ ድርጅት GIZ  regional value chain ኃላፊ አቶ ያሬድ ፈቃደ በበኩላቸው ልዑኩ  በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት፣በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ፣በስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በኮሪደር ልማት ተሞክሮዎችን በመቅሰም ለማስፋት ያለመ ጉብኝት ማድረጉን ገልፀዋል።

በጉብኝቱም መልካም ተሞክሮዎች ማግኘት መቻሉን የተናገሩት ኃላፊው ከሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የማስፋት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ጄኔራል ዊንጌት ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ2030 የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ይገኛል ያሉት የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ መለሰ ይግዛው ኮሌጁ በዘርፉ ባካበተው ልምድ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ልምዱን እያጋራ ይገኛል ብለዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘርፉን እሳቤ ወደ ተግባር በመቀየር በተሰራው ስራ ተወዳዳሪነቱ እያደገ መምጣት መቻሉ እና  የኮሌጁ አሰልጣኞች  ወደ ውጭ  ሀገራት በመሄድ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ መቻሉን አስረድተዋል።

በጉብኝቱ ከሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት፤ከቦትስዋና እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበር የተውጣጡ  የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም


.

Copyright © All rights reserved.